የቅድስት-አርሴማ-ገድል
የሕዳር ገድለ አርሴማ
አንድ አምላክ በሆነ፤ በአብ ፤ በወልድ ፤ በመንፈስ ቅዱስ ስም።
፩. ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማዕት የሆነች የብፅዕት የቡርክት፤ የክብርት ቅድስት አርሴማና
፪. በላያቸው ያለውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስትስን የኀይል ብርታት እያዩ፤ በሚያረጅ ሥጋቸውም ነዋሪ በሆነ ነፍሳቸው የትዕግሥትን ብርታት ያሳዩ ዘንድ፤
፫. የወንጀለኞችን ስሕተቶችንና መከራቸውን እየናቁ፤ የዚህን ዓለም መከራዎችንም እያቃለሉ፤ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ያዘጋጀውን። የማያረጀውንና የማይጠፋውን መልካሙን የዘላለም የኑሮ ብዛት ጣዕምን ያገኙ ዘንድ በብዙ ገድልና ትዕግሥት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ከእርስዋ ጋር ሰማዕት የሆኑ የሃያ ሰባቱ ሰማዕታት ገድልና ሰማዕትነት ይህ ነው።
፬. ስለዚህ እግዚአብሔር ከእነዚህ ሃያ ሰባት ሰማዕታት በረከት ይስጠን፤ ከብፅዕት ቡርክት ቅድስት አርሴማም የረድኤት ኀይል ያድለን። የቅድስት አርሴማ ጸሎትና በረከት ከሁላችን ጋራ ለዘላለሙ ይኑር አሜን።
፭. ከዚህም የብፅዕት ቅድስት አርሴማን የልደትዋን መነሻ እንናገራለን።
፮. በዚያን ዘመንም ክቡራን ከሆኑ ካህናተ ፤ ሌዋውያንና ከኀያላን ነገሥታት ወገን የሆነ ስሙ ቴዎድሮስ የሚባል አንድ ሰው ነበር።
፯. ከቤተ ክርስቲያን ሹሞች ካህናትና ሃይማኖታቸው የቀና ከሆኑ ከጳጳሳት አለቆች ወገን ስሟ ቡርክት አትኖስያና የምትባል ክብርት የሆነች ሴትን አገባ።
፰. እነርሱም እግዚአብሔርን የሚፈሩ ጻድቃን ነበሩ። በጾምና በጸሎት፤ በልመናና በስግደት፤ በትጋት የጸኑ ነበሩ። ሁል ጊዜም በትዕግሥትና በንጽሕና ይጋደሉ ነበር። በጸሎት፤ በቍርባንና በማዕጠንትም ጊዜ ወደ ቤተ ክርስትያን ይገሠግሡ ነበር። ነገር ግን ልጅን መውለድ ተሳናቸው። እስከ እርጅናም ድረስ መኻን ሆኑ።
፱. ስለዚህም ቡርክት አትኖስያነናታዝን፤ ታለቅስ ነበር። መወለድ ተስኖአታልና። በብዙ ኀዘንም ጌታዬ፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ መልካም ፍሬ፤ ወንድ ልጅን ወይም ሴት ልጅን ስጠኝ እንጂ፤ ፍሬ የሌለው ከንቱ እሆን ዘንድ፤ አታድርገኝ አንተ ከወደድክ ፤ ሁሉ ይቻልሃልና፤ የሚሳንህም የለምና። እያለች ዘወትር ወደ እግዚአብሔር ትጸልይ ነበር።
፲. ስለዚህም በሰማይና በምድር የሚኖር ፍሬ ስጠኝ። በምድር የሚኖር ፍሬ የፈቀድክልኝ ከሌለ፤ በሰማይ የሚኖር ፍሬ ስጠኝ። በሁለት ሥራ አትቅጣኝ። ጌታዬ አምላኪዬ መድኀኒቴ፤ ነፍሴን ይቅር በላት። ከአለኝታየም አታሳፍረኝ። የሚያስደስትህን አደርግ ዘንድ ለዘላለም የሚኖር ፍሬ ስጠኝ።
፲፩. ጌታዬና አምላኪዬ ሆይ የተናቀችና የተቸገረች፤ ያዘነችና የተከዘች እኔን ባርያህን ቸል አትበለኝ። በጥበብህ ኀይል ሰማይንና ምድርን፤ ባሕርንና በውስጧ ያለውን ሁሉ የፈጠርህ እግዚአብሔር አምላኪዬ ሆይ አትጸየፈኝ።
፲፪. በመልካም አገልግሎት በመመስገኛህ አዳራሽ የሚያገለግሉ የቅዱሳን አባቶቻችን የሚቃጠል መሥዋዕታቸውን፤ የቍርባናቸውንና የዕጫናቸውን መዓዛ የተቀበልህ ሆይ ! በማኅፀንዋ የተሸከመችኝን የእናቴን እንባ ያን ጊዜ አስብ። ለእናቴ የበኸር ልጇ ነኝና።
፲፫. በብዙ ልቅሶና ኀዘን በትጋት፤ በትሕትና፣ ለችግረኞችና ለጦም አዳሪዎች በመመጽወት እንደዚህ ስትጸልይ፤ እግዚአብሔር የልቧን ብርታት በአየ ጊዜ ስለ እርስዋ ይጸልይ ዘንድ ስሙ ልድዮስ የሚባለውን የቂሣርያ ሊቀ ጳጳሳት ወንድሟን አዘዘው።
፲፬. እርሱም ስለ እርስዋ ጸለየ። በመልካም ጠባይዋ እጅግ ይወዳታልና። ስለዚህም እግዚአብሔር የጳጳሳቱን አለቃ ጸሎትና የቡርክት አትኖስያና ልቅሶን
፲፭. መልኳ ያማረ፤ የምታስፈራ ያችን ልጅ ሰጣት። ይህችውም ቅድስት አርሴማ ናት። እሰከ ሦስት ዓመትም ድረስ አሳደገቻት።
፲፮. ከዚህም በኋላ አምላክን በወለደች በእመቤታችን ማርያም ስም ለተሠራች ቤተ ክርስቲያን ታገለግል ዘንድ ሰጠቻት። ከአሥራ ሁለት ዓመትም በኋላ አባትና እናትዋ ከካህናት ወገን የሆነ መልካም ጎልማሳን ያጋቡአት ዘንድ ወደዱ።
፲፯. ይህች ቅድስት አርሴማ ግን ይህን አልወደደችም ነበር። ነገር ግን እንደ ሕጋቸው ሠርግ አድርገው በእርሷ ሠርግ ታላቅ ደስታን ተደሰቱ። የብፅዕት ቅድስት አርሴማ የፊቷ ውበት ዕፁብ ድንቅ ነውና። በዚያን ዘመን በዚያ አገር ውስጥ ከፊትዋም ሆነ ከኋላዋ በመልክና በውበት የሚመስላት የለም። ይህን ዓለም በመናቅ ክርስትስን ከተከተሉት ቅዱሳት ደናግል አንስት እመቤትና የእውነት ፀሐይ ከሆነችው ከእመቤታችን ማርያም በቀር፤
፲፰. አሥራ አምስት ዓመት ከሆናት በኋላ ከሐዲውን ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስን ሰይጣን አነሣሣው። ከሐዲው ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ሚስት ያገባ ዘንድ፤ በመልኳ ውብ የሆነች ሴት ልጅን ፈለገ። መልኳ ውብ የሆነች አንዲት ሴት ልጅን ይመርጡለት ዘንድ በሀገሩ ሁሉ እንዲሄዱ በሰሌዳም መልክዋንና ቅርጽዋን ሁሉ ሥለው ይገልጡለት ዘንድ ሠዐሊየዎችን አዘዘ።
፲፱. እነዚህም ሠዐሊዎች ወደ ሮሜ አገር በደረሱ ጊዜ አንድ የደናግል ገዳም አገኙ። በዚያም ያችን ድንግል ቅድስት አርሴማን አገኙአት። ይህች ቅድስት አርሴማም ደም ግባቷ ያማረ፤ መልክዋ የሚያስደንቀ ነበር። በዚያም በደናግሉ ገዳም ውስጥ በመልክ እንደ እሱዋ ያለ ቆንጆ የለም። በመልክም የሚመሳሰላት የለም። በዚያም ሠዐሊዎች ሥዕላን ሥለው ለንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ላኩ። ንጉሡም ሥዕሏን በአየ ጊዜ ፈጽሞ ተደሰተ። ስለ ሠርጉ ወደ እርሱ እንዲመጡ ሕዝቡን ይጠሩአቸው ዘንድ ወደ ነገሥታቱና ወደ መኳንንቱ ላከ።
፳. ደናግሉም ይህን ነገር በአወቁ ጊዜ አለቀሱ። ተነሥተውም እንዲረዳቸውና በድንግልና እንዲጠብቃቸው እግዚአብሔርን እየለመኑ ከዚያ ገዳም ወጡ። ወደ ንጉሥ ድርጣድስ የግዛት አገር ወደ አርመንያ ደረሱ። በምድረ በዳ ዋሻዎችም ተቀመጡ። ቍጥራቸውም ሰባ ስምንት ወንዶችና ሴቶች ፤ ከደናግል ወስጥ ሠላሳ ዘጠኝ ነበሩ። በትልቅ ችግርም ተቀመጡ። ምግባቸውን የሚያገኙ አልነበሩም። ከእነርሱም አንዲትዋ መብራት ትሠራ ነበር። ከዚህች ሴት ሥራም ይመገቡ ነበር።
፳፩. ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስም ቅድስት አርሴማን በፈለጋት ጊዜ አላገኛትም። ነገር ግን በምድረ አርማንያ እንዳለች ስለእርስዋ ሰማቅድስት አርሴማን ይዞ እንዲልክለት ወደ አርማንያው ንጉሥ ድርጣድስ መልእክትን ላከ እንዲህም አለው ጠብቅልኝ፤ ወደ እኔም ላካት። የቅድስት አርሴማንም ሥራ ለንጉሥ ድርጣድስ አስረዱት።
፳፪. በዚያን ዘመንም ንጉሥ ድርጣድስ ለላ።ት የሚሰግድ፤ ፀሐይንና ጨረቃን የሚያመልክ ነበር። ዳግመኛም የብልኀተኛ እጅ ሥራ የሆኑትን እንጨትንና ድንጋይንም ያመልክ ነበር። በቤቱም አስቀምጦ አማልክት ብሎ ይጠራቸው ነበር፡፡ እንደ ፈጣሪው እግዚአብሔር ያከብራቸው ነበር።
፳፫. ስለዚህም ነገር ከእርሱ ጋራ ለጣዖት እንዲሰግዱ በማስገደድ የአገሩን ሰዎች ያውካቸው ነበር። በልቡ ሰይጣን ገብቶአልና። በውስጡም መንፈስ ቅዱስ ስለሌለ እግዚአብሔርን ትቶታልና።
፳፬. ይህ ንጉሥ ድርጣድስም፤ በሦርያ አገር ከደማስቆ ጀምሮ እስከ ቂሣርያ ወንዝና አፍራጦስ ድረስ የሾመው ስሙ ጤልሜዎስ የሚባል ገዥ ነበረው። እርሱም እንደ ነጣቂ ተኵላ ነበር። የአለቃውን ትእዛዝ ለመፈጸም ከክርስቲያን ወገኖች ያገኘውን ሁሉ ለጣዖት እንዲሰግዱ ያስገድዳቸው ነበር።
፳፭. እንዲሁም የክርስቲያን ወገኖችን ለርኵሳን ጣዖታቱ ያሰግዳቸው ዘንድ ይይዛቸው ጀመር።
፳፮. ብዙዎችንም በማስገደድ ያስታቸው ነበር። ስለክርስቶስ ፍቅርም ከክርስቲያኖች ለጣዖት ይሰግዱ ዘንድ እንቢ ያሉ ነበሩ።
፳፯. እነዚህንም ይመሰገንባቸው ዘንድ ወደ ንጉሡ ድርጣድስ እስከሚወስዳቸው ድረስ በእሥር ቤት ያሠሩአቸው ዘንድ አዘዘ።
፳፰. ከዚህም በኋላ በእሥር ቤት የታሠሩትን አወዋቸው። ሌሎችንም በቂሣርያ የያዛቸውን እጃቸውን በሰንሰለት አሥሮ ብአለንጋና በብትር ይገርፋቸው ጀመር።
፳፱. ቅድስት አርሴማ ግን፤ በአዳራሽዋ ሰገነት ትጸልይ ነበረች። መጻሕፍትዋንም እንደ ልማዷ ታነብ ነበር። የምታነበውንም፤ ቃል ለመበተን ብቻ አይደለም። አንብባ በየአገሩ ቋንቋ ለመተርጎም ነበር እንጂ፤ ለመስማት በሚቻል መጠን በአስተዋይ ልቡናም ትገነዘበው ነበር።
፴. ሐዋርያው፤ ሕግን ሁሉ የሚሠራ በአንዲትዋ ቢስት በኑሮው ውስጥ ወንጀለኛና በደለኛ ይሆናል እንዳለው፤
፴፩. ይህች ቅድስት አርሴማም የመጻሕፍትን ሕጎች በጥንቃቄ ትጠብቃቸው ነበር።
፴፪. ያን ጊዜም ብፅዕት አርሴማ እነዚህን ሰማዕት ሲገርፉአቸው በአየቻቸው ጊዜ ስለ እነሱ ጠየቀች። ስለ ክርስቶስም እንደሚገረፉ ነገርዋት።
፴፫. ያን ገዚም እንባዋን ከዓይኖቿ በፊቷ ላይ አፈሰሰች። ስለ እነዚህ ሰማዕት ትጸልይ ዘንድ በልብ ጭንቀት ወደ ሰማይ አንጋጠጠች።
፴፬. ከዚህ በኋላ ከእግዚአብሔር ዘንድ ተገልጦላት የብርሃን አክሊል የያዙ ብሩሀን መላእክትን አየች። ለእነዚህ ሰማዕት ይሰጧቸውና ይሸልሟቸው ዘንድ፤
፴፭. ያን ጊዜም ብፅዕት ቅድስት አርሴማ በታላቅ ቃል እየጮኸች ፤ ስለ ቅዱሰ ስምህ ሰማዕት እሆን ዘንድ፤ ጌታዬና አምላኪዬ ሆይ ርዳኝ፤ እያለች ከቤቷ አዳራሽ ሰገነት ወረደች።
፴፮. ከዚያም በኋላ ልብሷን ለብሳ ወደ እነርሱ ሄደች። ብፅዕተ ቅድስት አርሴማ በቀረበች ጊዜ ገዡ ጤልሜዎስ አያት።
፴፯. በአያት ጊዜም ደነገጠ። ልቡም ታወከ። ወደ ቤትም ትሄድ ዘንድ አዘዘ። ዳግመኛም የሚገርፉአቸውንም ይተዉአቸዉ ዘንድ አዘዘ።
፴፰. እመቤቴ ቅድስት አርሴማ ሆይ ምን ሆንሽ። የመልክሽስ ውበት ይህን ያህል ሲሆን ከዚህ ምን አመጣሽ፤
፴፱. ብፅዕት ቅድስት አርሴማ ሆይ አንቺ በሁሉ የተሸለምሽ ሲሆን ከቤትሽ ሰገነት ያወጣሽ ሥራ ምንድን ነው፤ ለመከራስ ወደ እኛ ትመጪ ዘንድ ያሰጨነቀሽ ምንድን ነው።
፵. አንቺ የያዛችኋቸውን ስለ እኔ ተውአቸው ብትዪ ፤ እኔም ከግርፋታቸው ስለ አንቺ እተዋቸዋለሁ። የምትወጃቸውን ሌሎችንም አላት።
፵፩. ያን ጊዜም ብፅዕት ቅድስት አርሴማ ቅድስት ቀኝና ግራዋን ደረትዋንና ሰውነቶቿን ሁሉ በትእምርት መስቀል ፊትዋን አማተበች።
፵፪. ገዥውንም ትሰድበው ጀመር። እንዲህ እያለች፤ አንተ ዝንጉና ወንጀለኛ እነዚህን የጨከኑ የክርስቶስን ሰማዕታት ስለ እኔ በምን ትተዋቸዋለህ። እነሱስ ለክርስቶስ ስም ሰማዕት ይሆኑ ዘንድ የተዘጋጁ ናቸውብሩህ የሆነ የመንግሥተ ሰማያት አክሊልም ተዘጋጅቶላቸዋልና።
፵፫. እኔም በጌታዬና በአምላኪዬ እስከምመሰገን ድረስ የእነዚህን ቅዱሳን ሰማዕት መከራዎችን እሸከም ዘንድ እወዳለሁ። በእግዚአብሔር አምላኪዬ ዘንድ፤ የእነርሱን የክብር አክሊል አገኝ ዘንድ፤
፵፬. ነገር ግን፤ በሥጋየ የእነሱን መከራ እቀበል ዘንድ የእነዚህ ቅዱሳን የበረከት ነጠብጣብና የአምላኪዬ የምሕረቱ ጸጋ ይድረሰኝ። ሞቴም ሕይወቴም ከእነርሱ ጋራ ትሁን አለች።
፵፭. እኛንም እንደነርሱ ጌታችን አምላካችን በሰማያት ለአለው የመንግሥት ክብር የተዘጋጀን ያድርገን።
በብፅዕት ቅድስት አርሴማም የረድኤተ ኀይል ከገሃነም እሳት ያድንነን። ለዘላለሙ አሜን።